‎የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ቢሮ “ብሩህ አዕምሮ፤በክህሎት የበቁ ዜጎች” በሚል መርህ ሀሳብ ያካሄደው የቴክኖሎጂ፣ የክህሎት እና የጥናትና ምርምር ውድድር ለአሸናፊዎች እውቅና በመስጠት ተጠናቅቋል። የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዮት ደምሴ በክህሎት፣ በቴክኖሎጂ እና በጥናትና ምርምር ዘርፎች የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ተወዳዳሪዎች ክልሉ እውቅና መስጠቱን ጠቁመዋል።

‎አንደኛ በመውጣት ያሸነፉ ተወዳዳሪዎች ቀጣይ በሀገር አቀፍ ውድድር ተሳታፊ ይሆናሉም ብለዋል። ተወዳዳሪዎች ያቀረቡት ስራ ለማህበረሰቡ እና ለክልሉ ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበው፤ የተቋማትን አቅም ለመገንባት ቢሮው በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

‎የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ቢሮ ም/ኃላፊ አቶ በዛብህ ገበየሁ ውድድሩ ቀጣይ በትኩረት ለመስራት መነሳሳት እንደፈጠረ አንስተው፤ በየደረጃው የሚገኙ ተቋማት በቴክኖሎጂ፣በክህሎት እና በጥናትና ምርምር ዘርፎች መትጋት እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል።

‎የአርባምንጭ ፖሊ ቴክኒክና ሳታላይት ኢንስቲትዩት ዲን አቶ በዛብህ ባርዛ ከኢንስቲትዩቱ 13ተወዳዳሪዎች በሀገር አቀፍ ውድድር ለመሣትፍ መመረጣቸውን አስታውቀው፤ የተሻለ ውጤት እንደሚጠበቁም ተናግረዋል። በውድድሩ የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ እና አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት እውቅና በመስጠት መርሃ-ግብሩ ተጠናቅቋል።