የቴክኖሎጂ፣ የክህሎትና ተግባራዊ ጥናትና ምርምር ላይ ያተኮረ ክልል አቀፍ ውድድር በአርባምንጭ እና በወላይታ ሶዶ ከተሞች ተጀምሯል፡፡የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ሀገሪቱ የጀመረችውን የመበልፀግ ራዕይን በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እያገዙ እንደሚገኙ ይነገራል፡፡የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮም በስሩ የሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን በማደራጀት ብቁና ተወዳዳሪ ወጣቶችን ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ውስጥ የድርሻውን በመወጣት ላይ ይገኛል ተብሏል፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዮት ደምሴ በውድድሩ መክፈቻ ላይ ተገኝተው እንደተናገሩት፤ በዝቅተኛና መካከለኛ ደረጃ ብቃት ያላቸውን ባለሙያዎችን ማፍራት የቢሮው ተቀዳሚ አላማ ነው፡፡ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልልም በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ፈጠራና አቅርቦት ረዥም ልምድ ያለው ነው ያሉት አቶ አብዮት፤ በምስራቅ አፍሪካም ተወዳዳሪና አሸናፊ ተቋማትን መፍጠር መቻሉንም አስታውሰዋል፡፡

ይህ በአርባ ምንጭ እና በወላይታ ሶዶ ከተሞች የሚካሄደው የክህሎት ውድድር በሀገሪቱ ብሎም በክልሉ ለሚገኙ እንዱስትሪዎች ብቁና አስተማማኝ ባለሙያዎችን ለማቅረብ ያግዛል ያሉት ደግሞ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ የቴክኖሎጂ ሽግግርና ኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት ወ/ሮ አበራሽ አለሙ ናቸው፡፡

በውድድሩ ላይ ከሚሳተፉ ወጣቶች መካከል ተማሪ ነጻነት ማቴዎስና ሄኖክ ተስፋዬ በበኩላቸው፤ ውድድሩ የእርስ በርስ የእውቀት ሽግግር ከመስጠቱም በዘለለ እውቀታቸውን የሚያዳብሩበት ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡ ክልላዊው የክህሎት ቴክኖሎጂ፣ ጥናታዊ ምርምርና ኤግዚቪሽን ከሚያዝያ 15 ጀምሮ ለተከታታይ ቀናት ይካሄዳል፡፡